11/09/2026
“ የምሕረት ዓመት ፳፻፲፱”
የተወደዳችሁ የፈውስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤተሰቦቻችን !
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እያንዳንዱ መንገድ የራሱ የትመጣ አለው። ከእነዚህም አንዱ“ ዓመተ ምሕረት” የሚለው አነጋገር ነው። በዓመት በዓመት ይህንን ያህል ዓመተ ምሕረት እያልን እንቆጥራለንና ። ለመሆኑ ግን ዓመተ ምሕረት የምንለው ለምንድን ነው ?
፩. በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስለተደረገልን ነገር
እግዚአብሔር ፍጥረትን ሲፈጥረው በልግስናው እንደ ፈጠረው እናውቃለን። ከፍጥረቱ አንዳች የሚጠቀመው ነገር የለምና። ምንም የማይረባ የማይጠቅመውን ፍጥረት በመፍጠሩም ፍጹም ቸርነቱና ለጋስነቱ ታወቀ። ከዚህ ሁሉ የሚያስደምመው ግን ለሰው ልጆች ያደረገው ሲሆን ይኸውም የገዛ መልኩን ሰጥቶ መፍጠሩ ነው። በአርአያውና በአምሳሉ ስላከበረውም ምድርና መላዋን ይገዛ ዘንድ የጸጋ ንጉሥ ሆኖ ተሾመ። ለፍቅር ምልክትነትና ለፈጣሪና ፍጡር ድንበርነት አንዲት እንጨት ብቻ እንዲያከብር ተሰጠው። ነገር ግን የወዳጅ ጠብ ጽኑዕ ሆነና ከፍጥረት ለይቶ ያከበረው የሰው ልጅ ሰማይና ምድር የማይችሉትን በደል በደለ። የፈጣሪውን ፍቅር ከማፍረሱ ፣ ያከበረውን አምላክ በአንዲት እንጨት እንኳ ታምኖ ካለማክበሩም በላይ መንግሥተ እግዚአብሔርን እስከ መተካከል ተመኝቶ የሞትን ፍሬ በላ። የሞት ሞትም ተፈረደበት። እግዚአብሔር ግን እንደ ፈረደበት ይቀር ዘንድ አልወደደም። ቀድሞም ፍቅሩን የሚገልጽበትን ነገር ሲሰጠው እንጂ የአንድ እንጨት ፍሬ ከልክሎት አልነበረምና። ያንን ፍቅር አንድ ልጁን እስከ መስጠት ገለጸ። ሰው በድሎ ሰው መካስ ሲገባው ሰው በድሎ እግዚአብሔር ክሶ ታረቀን። ሰው ከሰው ሲታረቅ ገንዘብ ይሰጣል ፣ሰው ከእግዚአብሔር ሲታረቅ እግዚአብሔር ግን የገዛ ልጁን ሰጠ ፣ ወልድም ራሱን ለሕማም ለሞት አሳልፎ ሰጠ። ሮሜ ፭፥፲ በዚህ ዓለም ሥርዓት ሰው ለወዳጁስ እንኳ በጭንቅ ጊዜ አይገኝም። ክርስቶስ ግን ስለ ጠላቶቹ ሞተ። የእንጨት ፍሬን ከለከለን ብለን ከእባቡ ጋር ያማነው ቸሩ እረኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ቅዱስ ሥጋውን በመቁረስ ክቡር ደሙን በማፍሰስ ለወገኖቹ አሳልፎ ሰጠ። በገዛ ደሙም ዓለምን ዋጀ። የእርሱን መልክ ትተን ብንኮበልል የእኛን መልክ ይዞ ተከተለን። ባዝነን በተበተንበት ሜዳ ወርዶ ፈለገን፤ ባገኘንም ጊዜ በትከሻው ተሸከመን አዳነንም። ማቴ ፲፰ ፥ ፲፩ ባሮቹ ለመባል የማይገባን ስንሆን የእኛ ወገን ይሆን ዘንድ የባርያን መልክ ገንዘብ አደረገ። ከእኛ ተወልዶ እኛን ዳግመኛ ወለደን። የልጅነትን ሥልጣን ሰጥቶ እርሱን ለብሰን አባ አባ ብለን በልጅነት እንድንጠራው ፈቀደልን። ልጆቹ በመሆናችንም ወራሾቹ የመሆን ሥልጣንን አጎናጸፈን። እነሆ ይህ የምሕረት ዝናም ለዓለማት ሁሉ ከወረደ እነሆ ፳፻፲፱ ዓመታት ሞሉት። ይህ ምሕረት ትናንት ተደርጎ የሚተረክ ሳይሆን ትናንት ራሱ አሁን ሆኖ በጸጋ የሚታደሉት እውነት ስለሆነ እያንዳንዱን ዓመት ዓመተ ምሕረት እንለዋለን።
፪. እያንዳንዱ ዓመት በምሕረት ስለሚሰጠን
ከሰዎች ጋር ስንኖር የቱንም ያህል ቢወዱን የማንለወጥ ከሆነ የሚሰለቹበት፣ የሚደክሙበት ፣ የሚማረሩበት ፣ ፊት የሚያዞሩበት ሲብስ ደግሞ ቆርጠው የሚለዩበት፣ አውጥተው የሚጥሉበት ጊዜ አለ። ለምን ብለን ብንጠይቃቸው “ ስንት ጊዜ ቻልኩ አሁንስ በቃኝ” የሚል መልስ ያስደምጡናል። እግዚአብሔር ግን በልጅነታችን ዘመን ባናፈራ እርሱን አሳልፎ የወጣትነትን ፣ በወጣትነቻንም ሳናፈራ የጎልማሳነትን፣ በዚህ ሳናፈራ እስከ ሽምግልና እየታገሠ ዓመታትን ይጨምራል። ታች የበቀሉትን አትክልቶች ከማጥፋት በቀር ፍሬ የማይሰጥን ቅጠል ብቻ የሆነን ተክል ሐያ፣ ሠላሳ ፣ ሐምሳ ዓመታትን የሚኮተኩት ይቅር ባይ የወይን ባለቤት መሐሪው አምላካችን እግዚአብሔር እንጂ ማን አለ ?ዘመናችንን ሁሉ ጎስቁለን ሌላ ዘመን የተሰጠን በምሕረት ዓይኖቹ ተመልክቶን ስለሆነ በምሕረትህ አንድ ዓመት ጨመርክልን እንጂ እኛስ መቆረጥ የነበረብን ፍሬ ቢሶች ነን ስንል ይህንን ያህል ዘመን ከነ ጉዳችን የተሸከመንን አምላካችንን ቀን በቆጠርን ጊዜ ሁሉ ዓመተ ምሕረት እያልን እናመሰግነዋለን።
፫.ምሕረት የምናገኝበት ዘመን ስለሆነ
ቀድሞ አባቶቻችን ነቢያት በመጋዝ እስከ መሰንጠቅ፣ ከአንበሳ ጉድጓድ እስከ መጣል፣ ከነደደ እሳት እስከ መወርወር ፣ በድንጋይ እስከ መወገር ደርሰው መከራ ቢቀበሉም፤ ለንጽሕናቸው እስከ መታሰር ቢደርሱም ፣ እነ ቅዱስ ዳዊትን የመሰሉት አልጋቸውን በእንባ እስከማራስ ደርሰው ቢያለቅሱም ግን በዚህ ሀሉ አንዳቸውም ምሕረት አግኝተው ከሲኦል ወጥተው ገነት አልገቡም። አሁን ግን ሰው በቀዝቃዛ ውኃ የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል ፤ ያም የሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ነው። ቀድሞ ይህንን ምሕረት ለማግኘት የጊዜ ቀጠሮ ነበረበት “ የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ ” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። ገላ ፬፥፬ ዛሬ ግን እያንዳንዱ ሰው በእያንዳንዷ ደቂቃ የመንግሥተ ሰማያትን ፍሬ ማፍራት ይቻለዋል። ቢፈቅድ በመጣበት ሰዓት ሁሉ የተከፈተ በር አለለት። ይኸውም የንስሐ ደጅ ነው። ክርስቶስ ሰዎችን በመጡበት ጊዜ ሁሉ እንደገና ራሱን አስመስሎ የሚወልድባት ማኅፀን ንስሐ ናት። አሮጌው ሰውነታችን በንስሐ ተጥሎ አዲስ ክርስቶስን የምንስመስልበት ዓመት ውስጥ ስለምንገባ አዲስ ዓመት ማለታችንም ስለዚህ ነው። እያንዳንዷ ደቂቃ አሁን ምሕረት ለማግኘት የተሰጠች ሀብት ናት። መንግሥተ ሰማያት አሁን በውሎ አዳራችንና በመውጣት በመግባታችን ውስጥ አለች። ክርስቶስ መንግሥተ ሰማያትን ከዘመናት በኋላ ሳይሆን ዛሬ በእያንዳንዳችን ቤት አቅርቧታል። ከዛሬም አሁን የመንግሥተ ሰማያት ሰዓት ነው።
የተወደዳችሁ የቤተ ጉባኤያችን የፈውስ መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን የወንጌል ማዕድ እድምተኞች ሌላ የመማር ፣ የመንጻት ፣ የይቅርታ ፣ አዲስ ሰው የመሆን ዓመት ዘመነ ሉቃስ ተጨምሮልናልና እንኳን ደስ አላችሁ።
የተወደዳችሁ ኦርቶዶክሳውያን ወንድሞቻችን ባለፈው ዓመት የሆስፒታል ግንባታ አስተዋውቀን እናንተም እየለገሳችሁ ፕሮጀክታችን እንደ ቀጠለ እንደሆነ ትገነዘባላችሁ።ነገር ግን ይህ የቤተ ጉባኤያችንን ሐዋርያዊ አገልግሎት የሚመለከት ፕሮጀክት ሲሆን በመሃል የቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ስላፈሰሰ ፣ የቅድስት ቁስቋም የእናቶች ገዳም ልትፈርስ ስለተቃረበችና አባቶችና እናቶች ለመኖር የሚያሸቸውን ፕሮጀክት ለማሟላት ሰሞኑን የገቢ ማሰባሰቢያ አድርገናል። በዚህ ገቢ ማሰባሰቢያ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት ተሰብስቦበታል። በተለይ ሀገራችን ኢትዮጵያ በማንነት ሽኩቻ አዙሪትና ማዕበል በምትናጥበት በዚህ ወቅት ከአራቱ ማዕዘን እየደወላችሁ ክርስትናንም ኢትዮጵያዊነትን በመግለጻችሁ ደስታችን ዕጥፍ ድርብ እንደሆነ አንገልጻለን። ይህ ብቻ ሳይሆን ከእስልምናም ከፕሮቴስታንም እምነት ተከታዮች ጭምር በገቢ ማሰባሰቢያው ጭምር መሳተፋቸው ለሁሉ የሚያጠግብ ጡቶች ያሏት እናታቸንን ኢትዮጵያን ተመልክተንበታል። አዎ የሚያምርብን ይህ ነው! የትክክለኛዋ ኢትዮጵያ መልክ ይህ ነው። ሰው በእምነቱና በቋንቋው አንድ ባይሆን በሰውነቱ የሚዋሐድባት ሀገር ኢትዮጵያ። በዚህም እንደ ክርስትና ለድኅነት ፣ እንደ ሰው ለምክርና ለጨዋነት፣ ለበጎነት ለምታዳምጡን ሁሉ ማዳመጣችሁንም ያላችሁንም የሌላችሁንም በመስጠት ፍቅራችሁን ለገለጻችሁልን ኦርቶዶክሳውያንና ኢትዮጵያውያን ኤርትራውያን ጭምር ከደቀ መዛሙርቱና ከመናንያኑም ጋር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንወዳችኋለን። አዲሱን ዓመት ገዳማችንን ሠርተን ስለተሻገርን አምላከ አበው እናንተንም ወደ በጎ ምዕራፍ ያሻግራችሁ። አብራችሁን ለሰነበታችሁ መምህራን ፣ ዘማርያን፣ ቤተ ክርስቲያን ስትጠራችሁ አቤት ብላችሁ ለመጣችሁ የዓለም ጥበብ ባለሙያዎች ልጆቻችን ሁሉ ዘመናችሁ ይባረክ።
ልክ በገቢ ማሰባሰቢያው እንደታየው ሁሉ ምሕረት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ጊዜ አሁን ነው። ጭካኔያችንን ሰማይና ምድር በድርቅ እስኪሰከሩብን ደርሷል። ታሪክን ለመታረቅ እንጂ ለመወቃቀስ ከተጠቀምንበት የሚወቀስበት ታሪክ የሌለው ግለሰብም ሆነ ቡድን አይገኝም። ግን የሚያስታርቀንን ከፈለግን ከሁሉም ቦታ ድንቅ የጥበብ ስብጥርና ውበት አለ። ድንጋይ እየፈለጉ በፈረሰው በኩል እየገጠሙ ሀገርን መሥራት እንጂ በእያንዳንዱ ቤት ቀዳዳ ከተፈለገ ግን መፍረስ እንጂ መታነጽ አይገኝም። በሀገራችን ቤት ሲቃጠል የሰፈሩ ሰው ሁሉ አንዳንድ እንጨት አዋጥቶ ይሠራዋል። አሁንም በሁሉም ግለሰብና ኅብረት ውስጥ በጎ እንጨት ይፈለግ፣ አታስፈልግም የሚባል ሳይኖር እስከ ትንሿ ሐረግም ድረስ ተፈልጎ ኢትዮጵያዊነት ይሠራ። ትናንት የተበዳደልንበትን ትተን የተረዳዳንበትን ፈልገን እንኑር። ኢትዮጵያ ለእኛነት እንጂ ለእኔነት አትመችም፤ አልለመደባትምም። ይህንን ጽሑፉ ስጽፍ በኅሊናየ ያሰብኩት ኢትዮጵያን እንጂ እገሌንም ሆነ እነ እገሌን አይደለም። ቅኔም የለውም።
እግዚአብሔር ትናንታችን ቢቆጥር ኖሮ እንኳንስ ዓመት ዕለትም ባልጨመረልን ነበር። ትናንትን በምሕረት ትቶ ሌላ ዓመተ ምሕረት እንደ ጨመረልን የተጠማመድንበትን ትተን የሚያዋሐደንን ፈልገን በምሕረት የምንከርምበት ዓመት ይሆንልን ዘንድ ዓመቱን ከግለሰብ ጀምሮ በይቅርታ እንጀምር ዘንድ እጆቿን በዘረጋችለት በኢትዮጽያ አምላክ እማጸናለሁ ።
ውድ ኢትዮጵያውያን እኔም ወንድሞቼ ደቀ መዛሙርትም እንኳን አደረሳችሁ ብለናል። አብረን ስንማማር እንከርም ዘንድ ቤተሰቦቻችን ስለሆናችሁ ደስ ይለናል። የቸርነት ባለቤት ዘመንን ከነ ፍቅሩ ያድለን ።
ሐዋርያዊ ትምህርትን በመጠበቅ ዘመንን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጋር እንሻገር
አባ ገብረ ኪዳን ግርማ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት የርእሰ ገዳማት ወአድባራት ጣና ቅዱስ ቂርቆስ አንድነት ገዳም የ፬ቱ ጉባኤያተ መጻሕፍት ምስክር መምህር